#መቋሚያ - የሙሴ በትር ምሳሌ ነው። - መቋሚያው ከጫፉ ላይ ቀርነ በግዕ (የበግ ቀንድ የመሰለ) መኖሩ ክርስቶስ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ የእግዚአብሔር በግ ለመሆኑ ምሳሌ። - መቋሚያ የመስቀል ምሳሌም ነው። ሙሴ በበትሩ ባሕረ ኤርትራን እንደከፈለ የፈርዖን ሠራዊትን እንዳጠፋ ክርስቶስም በመስቀል ተሰቅሎ አጋንንትን አጥፍቷል በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን አድኗልና። - እግዚአብሔር ለአዳም ተስፋ አድርጎ የሰጠው የመስቀል ምሳሌ ነው። #ጸናጽል - የሰዋስወ ያዕቆብ የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። - በያዕቆብ የራእይ መሰላል መላእክት ይወጡባት ይወርዱባት እንደነበረ ለማመልከት ድምፅ የሚሰጡ ብረቶች የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው። - ጽናጽል ላዩ ቀስተ ደመና መስሎ መሠራቱ "እሰይም ቀስትየ በውስተ ደመና" ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው። (ዘፍ 9፥12) ብሎ በተናገረው መሠረት እግዚአብሔር ለኖኅ የገባለት ቃል ኪዳን ምሳሌ ነው። - አራቱ ዘንጎች የአራቱ ባሕርያተ ሥጋ (ነፋስ፣ እሳት፣ መሬት፣ ውሃ)፤ በአራቱ ዘንጎች ውስጥ ያሉት ቅጠሎች ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ የተፈጠረ ፍጥረት በሙሉ ምሳሌ ናቸው። - እነዚህም ሲንቀሳቀሱ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ የተፈጠሩትን ፍጥረታት ሰውንም አላጠፋም ብለህ ቃል ኪዳን ሰጥታሃልና ኪዳንህን አስብልን በኃጢአታችን አታጥፋን ብለው ማመስገናቸውን የሚያመለክት ነው። - መሰላሉ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ያየው መሰላል ምሳሌ ነው። - በግራና በቀኝ በሉት ዓምዶች መካከል ያሉት ሁለት ቀጫጭን ጋድም ዘንጎች፤ በዘንጎቹ ላይ ያሉት ቅጠሎች የመላእክታን፤ በቀኝና በግራ ያሉት ሁለቱ ዓምዶች የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ምሳሌዎች ናቸው። - አንድም ሁለቱ አግድሞች የፍቅረ እግዚአብሔር እና የፍቅረ ቢጽ/ሰው ምሳሌ ናቸው።
Dec 26, 2025