https://t.me/Enatachn_mareyam/5358
Nov 27, 2025https://t.me/Enatachn_mareyam/5358
Nov 27, 2025https://t.me/Enatachn_mareyam/5357
Nov 27, 2025+++ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። +++ + ኅዳር 22 ቀን + እንኳን በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ እጅ ሰማዕትነት ለተቀበሉ በድዮማ ከተማ አረምያ ከምትባል አገር ለሆኑ ለቅዱሳን ለቆዝሞስና ለድምያኖስ ለወንድሞቻቸው ለአላድዮስ ፣ለአቢሞስ ፣ለአብራንዮስና ለእናታቸው ለቅድስት ቴውዳዳ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱስ ቆዝሞስ ማኅበር ሰማዕታት ከሁለት መቶ ስልሳ ሁለት ወንዶችን፣ ከአርባ ዘጠኝ ሴቶችና ከቀሌምንጦስ ዕረፍት ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። +++ + "ሰላም ለቆዝሞስ ወድምያኖስ ወአላንዴዎስ ወአቢሞስ ወአብራንዮስ ወእሞሙ ቴውዳዳ ምልእት መንፈስ"። ትርጉም፦ በመንፈስ የተመላች ለእናታቸው ለቴውዳዳ፣ ለቆዝሞስ ለድምያኖስ ለአላዴዎስ፣ ለአቢሞስና አብራንዮስ ሰላምታ ይገባል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ። +++ + ቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ ወንድሞቻቸው አንቲቆስ፣ ዮንዲኖስና አብራንዮስ እናታቸው ቅድስት ቴዌዳዳ፦ እሊህም ድዮማ ከምትባል ከተማ ስለ እግዚአብሔር ልጅ የታነፀች ግምብ ከአለችበት አረምያ ከምትባል አገር ናቸው። እናታቸውም ቴዌዳዳ እግዚአብሔርን የምትፈራና የምትራራ መጻተኞችንና ድኆችን የምትወዳቸው የምትረዳቸው ናት አባታቸውም ከሞተ በኋላ ልጆቿን እያስተማረች አሳደገቻቸው። እሊህም ሁለቱ ቆዝሞስና ድምያኖስ የሕክምና ጥበብን ተምረው በሽተኞችን ያለ ዋጋ የሚፈውሱአቸው ይልቁንም ድኆችን አብዝተው የሚረዷቸው ሆኑ። ወንድሞቻቸው ሦስቱ ግን ወደ ገዳም ሒደው መነኰሱ በጾምና በጸሎትም ተጠመዱ። + ከአባ አጋግዮስ አደራ በአስጠበቀው በንጉሠ ቊዝ ልጅ ምክንያት ዲዮቅልጥያኖስ ክዶ የረከሱ ጣዖታትን በአመለከ ጊዜ በምዕመናን ላይ መከራ ሆነ ገንዘብ ወዳጅ አጋግዮስ ብዙ ወርቅን ተቀብሎ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ወደ አባቱ ልኮታልና ከዚህም በኋላ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ዲዮቅልጥያኖስ ዳግመኛ ከጦር ሜዳ አግኝቶ ማረከው እርሱንም ንጉሡን ልጅ ሠውሮ አባ አጋግዮስን ጠራው ያንንም አደራ የሰጠውን የንጉሠ ቊዝን ልጅ እንዲአመጣ አዘዘው አጋግዮስም ሙቶ ተቀብሮአል ብሎ በሐሰት ተናገረ በዚያንም ጊዜ በመሠዊያው ፊት አማለው እሳትም ከሰማይ ወርዳ እንደምታቃጥለው ጠበቀ የእሳትም መውረድዋ በዘገየ ጊዜ ወርቅን በእሳት አቅልጦ አጠጣውና አቃጠለው ስለዚህም ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጣዖታትን አመለከ። + ቆዝሞስና ድምያኖስ በአገሩ ሁሉ ስለ ክርስቶስ እነርሱ እንደሚያስተምሩ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ወደርሱ እንዲአቀርቧቸው አዘዘ በደረሱም ጊዜ ለአገረ ገዢው ለሉልዮስ እንዲአሠቃያቸው ሰጠው። እነርሱም በብዙ ሥቃዮች ማሠቃየትን ጀመረ በእሳት የሚያቃጥልበት ጊዜ አለ በግርፋት የሚገርፍበት ጊዜ አለ ሦስት ወንድሞችም እንዳሏቸው ሰምቶ እነርሱንም ወደርሱ አስመጣቸውና አምስቱንም በመንኰራኵር ውስጥ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ። ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨምሩዋቸው በውስጡም ሦስት ቀኖችና ሌሊቶች ኖሩ ያለ ጥፋትም በጤንነት ወጡ ዳግመኛም ከብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቻቸው እሳቱን አነደዱ እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት ጠበቃቸው። + መኰንኑም እነርሱን ማሰቃየት በሰለቸው ጊዜ ወደ ንጉሥ መለሳቸው ንጉሡም ዳግመኛ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ቴዎዳዳ እናታቸውም የምታስታግሣቸው ንጉሡንና የረከሱ ጣዖቶቹን የምትረግም ሆነች። በዚያንም ጊዜ አንገቷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች ሥጋዋ ግን በምድር ላይ ወድቆ ነበር ቆዝሞስም እንዲህ ብለሸ ጮኸ "የዚች አገር ሰዎች ሆይ ይችን አሮጊት መበለት ሥጋዋን አፈር አልብሶ ይሠውራት ዘንድ ከውስጣችሁ ርኅራኄ በልቡ ያደረበት የለምን?" የህርማኖስ ልጅ ቅዱስ ፊቅጦርም በሰማ ጊዜ ተደፋፍሮ ሥጋዋን ገንዞ ቀበራት። + ንጉሡም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ከመከራውም ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። +++ + "ሰላም እብል ለደቂቀ ቴውዳዳ ዘተንዕዱ። በበአስማቲሆሙ ለለአሐዱ። ዘኮነቶሙ ምኅባአ ለእግዚአብሔር በፈቃዱ። ማሕፀነ ምድር አምሳለ ሕፃናት ዘይትወለዱ። ለእሳት ግሩም እስከ ሐልቀ ነዱ"። ትርጉም፦ የሚያስፈራ እሳት ነበልባሉ እስኪያልቅ ድረስ በሚወለዱ ሕፃናት አምሳል የምድር ማሕፀን በእግዚአብሔር ፈቃዱ መሸሸጊያን የኾነቻቸው ለእያንዳንዳቸው የተከበሩ ለኾኑ ለቴውዳዳ ልጆች በየስማቸው ሰላም፡እላለኊ። አርከ ሥሉስ (አርኬ) የኅዳር22። +++ + የዕለቱ ምስባክ፦ "ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ78፥10-11። የሚነበበው፡ ወንጌል ማቴ10፥9-18። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል። ለሁላችን ይሁንልን።
Nov 27, 2025