🕊 † ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት † 🕊 (ጥር 16) - "ፊላታዎስ" ማለት "መፍቀሬ እግዚአብሔር እግዚአብሔርን የሚወድ እርሱም የሚወደው"(የአምላክ ወዳጅ) ማለት ነው:: ቅዱሱ የዘመነ ሰማዕታት [፫ኛው መቶ ክ/ዘመን] ፍሬ ሲሆን ለየት ያለ ታሪክ ያለው ቡሩክ ወጣት ነው:: - እርሱ የባለ ጸጐች ልጅ: ስለ ክርስትና ምንም ሰምቶ የማያውቅ ሕጻን ነበር:: ወላጆቹ የሚያመልኩት ላምን ሲሆን የአካባቢው ሰው ደግሞ ለጸሐይ ይንበረከክ ነበር:: ቤተሰቦቹ ስለ አምልኮ ሲጠይቁት "እናንተ የምታመልኯቸው ፍጡራን ስለ ሆኑ አልፈልግም" አላቸው:: - ሕጻን ቢሆንም ስለ ፈጣሪው ተመራመረ:: በመጨረሻውም ፀሐይን "አንተ ምንድነህ?" ቢለው "እኔ ፍጡር ነኝ" ሲል መልሶለታል:: በዚያች ዕለት ግን ቅዱስ መልአክ ወርዶ: ሁሉን ነገር አስተምሮ የክርስቶስ ወታደር አድርጐታል:: - ወደ ቤቱ ተመልሶም የወላጆቹን ላም "እውነትን ተናገር" ብሎ ገስጾታል:: ላሙም ሰይጣን እንዳደረበት በሰው ልሳን ተናግሮ: የቅዱሱን ወላጆች ወግቶ ገድሏቸዋል:: ቅዱስ ፊላታዎስ ግን ላሙን አስገድሎ: ወላጆቹን ከሞት አስነስቶ ከአካባቢው ሰው ጋር በስመ ሥላሴ አስጠምቁዋቸዋል:: - በድንግልና ኑሮም ዘመነ ሰማዕታት ሲጀምር በርጉም ዲዮቅልጥያኖስ እጅ ብዙ ተሰቃይቷል:: በጸሎቱም ጣዖታቱን [እነ አዽሎንን] ከነ አገልጋዮቻቸው ወደ ጥልቁ አስጥሟቸዋል:: እርሱም በዚህች ቀን በሰይፍ ተከልሎ ለክብር በቅቷል:: ለእኛ ለኃጥአን የሚሆን ቃል ኪዳንንም ከጌታው ተቀብሏል::
Sep 11, 2025