አላህ ልጅ ቢኖረው ሙሀመድ የአላህን ልጅ እንደሚገዛለት እንደሚያመልከው ተናግሯል! አላህ ልጅ ቢኖረው ልጁም ይመለክ ነበረ ማለት ነው? ሙሀመድ አመልከው ነበር ያለው ለምንድነው? ሙስሊሞችስ አላህ ልጅ ቢኖረው ታመልኩት ነበር? ለምን? «ለአልረሕማን ልጅ ቢኖረው እኔ ለልጁ #ከተገዥዎቹ መጀመሪያ ነኝ» በላቸው፡፡ ->የጌጣጌጥ ምዕራፍ ቁጥር 43
Jun 20, 2025ምንም እንኳን የእምነት ጉዳዮች ከፍ ያለ ስነ-ስርዓትና ማብራሪያ ሚያስፈልጉ ቢሆንም ለተጠየቀው ጥያቄ፣ እነሆ እንዲሁ መረጃ እቀርባለሁ፣ መነሻዬ የሚሆነው አክብሮት ነው🙏 በመጀመሪያም እስልምና በመሠረቱ አንድ አላህ እንዳለ ያምናል። እሱ ልጅ የለውም፣ ይህ በቁርዓን ውስጥ በግልፅ ተገልጿል። (ቁርዓን 112:1–4) አምላካችን አሏህ የባሕርይ ልጅ እንደሌለው ለማመላከት የተጠቀመበት ሐርፉ አሽ-ሸርጥ በመጠቀም ነው፥ "ሐርፉ አሽ-ሸርጥ" حَرْف الشَرْط ማለት "ሁኔታዊ መስተዋድድ"conditional particle" ነው፦ 43፥81 «ለአልረሕማን ልጅ ቢኖረው እኔ ለልጁ የተገዢዎቹ መጀመሪያ ነኝ» በላቸው፡፡ قُلْ إِن كَانَ لِلرَّحْمَـٰنِ وَلَدٌ فَأَنَا أَوَّلُ الْعَابِدِينَ "ኢን" إِن ወይም "ለው" لَوْ በሰዋሰው አቀማመጥ ሐርፉ አሽ-ሸርጥ ነው፥ እዚህ አንቀጽ ላይ "ኢን" إِن የሚለው የገባው ሐርፉ አሽ-ሸርጥ "አሏህ ልጅ የለውምና ስለዚህ ዒሣን አትገዙት" እንጂ "ልጅ ካለው መገዛት ይቻላል" የሚል በፍጹም አይደለም። ለዚህ አንቀጽ ተመሳሳይ አንድ የሙግት ናሙና እናቅርብ፦ 7፥143 ሙሳም ለቀጠሯችን በመጣና ጌታውም ባነጋገረው ጊዜ፡- *«ጌታዬ ሆይ! አሳየኝ ወደ አንተ እመለከታለሁና» አለ፡፡ አላህም፡- «በፍጹም አታየኝም ግን ወደ ተራራው ተመልከት፡፡ "በስፍራውም ቢረጋ በእርግጥ ታየኛለህ"» አለው፡፡ ጌታው ለተራራው በተገለጸ ጊዜ እንኩትኩት አደረገው፡፡ ሙሳም ጮሆ ወደቀ፡፡ በአንሰራራም ጊዜ «ጥራት ይገባህ፡፡ ወደ አንተ ተመለስኩ፡፡ እኔም የምእምናን መጀመሪያ ነኝ» አለ፡፡ وَلَمَّا جَاءَ مُوسَىٰ لِمِيقَاتِنَا وَكَلَّمَهُ رَبُّهُ قَالَ رَبِّ أَرِنِي أَنظُرْ إِلَيْكَ ۚ قَالَ لَن تَرَانِي وَلَـٰكِنِ انظُرْ إِلَى الْجَبَلِ فَإِنِ اسْتَقَرَّ مَكَانَهُ فَسَوْفَ تَرَانِي ۚ فَلَمَّا تَجَلَّىٰ رَبُّهُ لِلْجَبَلِ جَعَلَهُ دَكًّا وَخَرَّ مُوسَىٰ صَعِقًا ۚ فَلَمَّا أَفَاقَ قَالَ سُبْحَانَكَ تُبْتُ إِلَيْكَ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُؤْمِنِينَ እዚህ አንቀጽ ላይ "ኢን" إِن የሚለው የገባው ሐርፉ አሽ-ሸርጥ "ተራራው አይረጋምና ስለዚህ አታየኝም" እንጂ "ቢረጋ ታየኛለህ" ማለት እንዳልሆነ ሁሉ በተመሳሳይ ከላይ ያለውን አንቀጽ በዚህ ልክ እና መልክ መረዳት ይቻላል። "በስፍራውም ቢረጋ" ማለት "አይረጋም" ማለት ከሆነ "ልጅ ቢኖረው" ማለት "የለውም" ማለት ነው፥ በጥቅሉ "በስፍራውም ቢረጋ በእርግጥ ታየኛለህ" ማለት "አይረጋም አታየኝም" የሚለውን ለመግለጽ የመጣ ግነታዊ አገላለጽ እንደሆነ ሁሉ "ለአልረሕማን ልጅ ቢኖረው" ማለት "ለአልረሕማን ልጅ የለውም" የሚለውን ለመግለጽ የመጣ ግነታዊ አገላለጽ ነው።
Jun 20, 2025