አዳም ሄዋንን መቼ ነው ያወቃት? ፍቅርስ ግንኙነትስ የጀመሩት መቼ ነው ከኤደንገነት ውስጥ ወይስ ወደምድር ከተባረሩ ቦሀላ ??
Jun 10, 2025ፍጥረታትን በሰርክ በሰርክ ሲፈጥሩ የሰነበቱ ቅድስት ሥላሴ ዓርብ በነግህ ነውር ነቀፋ የሌለበትን ፍጹም መልካም የሆነን አዳምን ከመሬት አስገኝተውታል። ( ሥግው እመሬት ፤ ከመሬት የተገኘ ሰው ) ፈጥረውም ድካም ፤ ዕረፍት ፤ ንዋም( እንቅልፍ ) ፤ ንቃሕ(ንቃት) ፤ ትጋህ(ትጋት) የሚስማማው አድርገው ፈጥረውታል። ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለምም ሲሉ ሔዋንን ፈጥረውለታል። ( ዘፍ 2 ) አዳምን በነግህ ሲፈጥሩት ሔዋንን በሠለስት ( በሦስት ሰዓት ) ፈጥረዋታል (አክሲማሮስ)። አዳምም ከተፈጠረበት ቦታ አርባ ቀን ተቀምጧል። (ኩፋ 4 ) አዳም በተፈጠረም በአርባ ቀኑ በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን አሳድረውበታል። ( ዘፍ 2 ) ከዚኽም በኋላ ሥላሴ በባህርይ የገዙትን እሱ በጸጋ ገዛ። ሥላሴ በባህርይ ያዘዙትን እርሱ በጸጋ አዘዘ። ከዚኽም በኋላ መላእክት አዳምን የብርሀን መጐናጸፊያ አጐናጽፈው የብርሀን ጫማ አጫምተው የብርሀን ዝናር አስታጥቀው የብርሀን ዘውድ በራሱ ደፍተው በብርሀን ሠረገላ አስቀምጠው " ቅዱስ እግዚአብሔር ዘፈጠሮ ለአዳም " እያሉ በእልልታ በደስታ ወደ ገነት አስገብተውታል። ( ኩፋ 4 ) ሔዋንንም በሰማንያ ቀኗ እንዲሁ በገነት ከአዳም ጋር ጨምረዋታል። አዳምና ሔዋን ወደ ገነት ከመግባታቸውም አስቀድሞ ሥላሴ "ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት" ሲሉ ቡራኬንም ትዕዛዝንም ሰጥተዋቸዋል።(ዘፍ 1) ወደ ገነት ከገቡ በኋላ ስለ ምን አሏሏቸውም ቢሉ ገነት ሥጋዊ ሥራ ይፈጸምባታል ባሉ ነበር ከገነት ከተባረሩ በኋላስ ስለ ምን አላሏቸውም ቢሉ መውለድ መዋለድ መብዛት መባዛት በኃጢአት የመጣ ነው ባሉ ነበርና ቅድስት ሥላሴ አዳምንና ሔዋን በታላቅ ክብር ወደ ገነት ከማስገባታቸው በፊት ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት በማለታቸው ሩካቤ የራሱ የሆነ ጊዜና ቦታ እንዳለው ያሳየናል ! ! በዚኽም መሰረት አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ በነበራቸው የሰባት ዓመት ቆይታ ሩካቤ የፈጸሙ አልነበረም። አትብላ የተባለውን በመብላቱ እና ሕገ እግዚአብሔርን በመጣሱ ከገነት የተባረረ አዳም በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ ሲል ምንም እንኳ በሰላሳ አምስተኛው ቀን ቢወጣም ለአርባ ቀናት በሱባኤ ለመቆየት የወሰነ ሲሆን እግዚአብሔርም ንስሐቸውን ተቀብሎ ታርቋቸዋል። ከዚኽም በኋላ አዳም ሚስቱን ሔዋንን በመኝታ አውቋታል። (ሩካቤ ዘበሕግ) በአንድ ሩካቤ ሁለት በአስራ አምስት ሩካቤ ሰላሳ በሰላሳ ሩካቤም ስልሳ ልጆችንም ወልደዋል። . .. ከሚኮጵያ ጽሑፍ የተቀነጨበ
Jun 10, 2025