የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለጾም ሥርዓትና ደንብ አውጥታለች። በዓመት ውስጥ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት እንዳሉና ማንኛውም ክርስቲያን (ከሰባት ዓመት ጀምሮ)እነኚህን አጽዋማት እንዲጾም ታዛለች 1. ዓቢይ ጾም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ የጾመው ጾም ሲሆን ለእኛም አርአያ የሆነበት ነው። ይህም በማቴ4፥1-11 የተገለጸ ነው። ጌታ የጾመው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሲሆን እኛ ግን የምንጾመው 55 ቀናት ነው። 15 ቀናት የተጨመሩበት ምክንያት አለ በአብይ ጾም ውስጥ ስምንት ሳምንታት ይኖራሉ ከእነዚህ ቀናት ውስጥ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሁድ ይገኛሉ ፣ እነዚህም አስራ አምስት ቀናት ከጥሉላት (እንስሳት ተዋጽኦ ቅቤ ወተት ምናምን) እንጂ ሰንበት ስለሆነ በሰዓት ተገድቦ ስለማይቾም እነዚህን ለማካካስ ተጨምረዋል ዓቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት የጌታ ጾም ስለሆነና ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች ድል የተነሱበት ዛሬም ክርስቲያኖች የጌታን አርአያ ተከትለው ሰይጣንን ድል የሚነሱበት ጾም ስለሆነ ነው። 2. ጾመ ሐዋርያት ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስቅዱስ ተቀብለው የወንጌልን መልዕክት ለማዳረስ ወደ ዓለም ከመሰራጨራቸው በፊት ልክ አምላካቸው ኢየሱስ እንደጾመ ሁሉ እነሱም እሱን ምሳሌ በማድረፍ የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉት ጾም ነው ፤ መነሻው ከዕለተ ጰራቅሊጦስ (ከትንሳኤ ከ50 ቀን በኋላ ማለት ነው) መጨረሻው ሐምሌ 5 ነው 3. ጾመ ስብከት (ነብያት) ነቢያት የሚባሉትም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበሩ የአካላዊ ቃል ክርስቶስን መወለድ በጾምና በጸሎት ይጠብቁ፤ ትንቢት ይናገሩ፤ ሱባኤ ይቆጥሩ የነበሩ የቃልም የጽሑፍም ነቢያት ናቸው፡፡ አባታችን አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከፈጣሪው ተጣልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ ‹‹አልቦቱ ካልዕ ኅሊና ለአዳም ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ›› እንዲል አትብላ ያለኝን ዕፀ በለስ በልቼ ፈጣሪዬን አሳዘንኩት እያለ ሲያዝን ሲጸልይና ሲጾም ጌታ እግዚአብሔር ኃዘኑን አይቶ ጾም ጸሎቱን ሰምቶ "በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅኽ ተወልጄ ሰው ሰውኛን ኖሬ በመስቀል ተሰቅዬ በሞቴ አድንኃለኹ፡፡›› ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጥቶታል፡፡ (ቀለሜንጦስ) ከእርሱ በኋላ የተነሡ ነቢያት ይህንን ተስፋ ድኅነት ይዘው እኩሌቶቹ በፀሐይ እኩሌቶቹ በጨረቃ ሌሎቹም በከዋክብት ሱባኤውን ሲቆጥሩ ኖረዋል፡፡ ነገር ግን በጸለዩት ጸሎት በሠዉት መሥዋዕት መዳንም ኾነ ማዳን የማይቻላቸው ቢኾን ለአባታችን ለአዳም በሰጠው ተስፋ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በሕማሙ በሞቱ ዓለምን ያድን ብለው በየዘመናቸው ግብር ገብተው ቀኖና ይዘው በጾም በጸሎት ሲጠይቁ ኖረዋል፡፡ ጌታም የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ነውና አምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺሕ አምስት መቶ) ዘመን ሲፈጸም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ኾኖ በሠላሳ ሦስት ዓመቱ በዕለተ ዓርብ ተሰቅሎ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ያሉትን አድኗል፡፡ በመኾኑም ነቢያት ስለጌታ ሰው መኾንና ስለ ሰው መዳን የጾሙትን የጸለዩትን በማሰብ ከበዓለ ልደት አስቀድሞ ያሉትን ስድስት ሳምንታት እንጾማለን (ህዳር 15 - ታህሳስ 29)፡፡ ስለዚህ አሁን የገባው ጾም እየጾምን ያለነው ይኼንን ጾም ነው ማለት ነው 4. ጾመ ድኅነት የረቡዕ እና አርብ ጾም ነው ፤ ከሌሎቹ ቀናት ተለይተው የሚጾሙባቸው ምክንያት፡ ረቡዕ፡ የጌታ ምክረ ሞቱ ማለትም በአንድ ሰው ምክንያት የተነሳ ሕዝቡ ከሚታመስ አንድ ሰው ቢሞት አይጎዳምና ይሙት በቃ ብለው ተማክረው ሞቱን የፈረዱበት ዕለት ስለሆነ ዓርብ፡ ረቡዕ ያጸደቁትን ይሙት በቃ ፍርድ በዕለተ ዓርብ ተግባራዊ አድርገውታል ፤ እኛም በነዚህ ቀናት በጾም በስግደት ስለ ሲል የሞተውን አምላካችንን እናስባለን በዚህ ምክንያት ጾመ ድኅነት ይባላል 5. የነነዌ ጾም መሠረቱ የነነዌ ሰዎች የጾሙት ጾም ነው ፤ ዛሬም እኛ እንደእነሱ በኃጢአታችን እንዳንጠፋ ጌታ ምሕረቱን ይሰጠን ዘንድ የምንለምንበት ጾም ነው 6. ጾመ ገሃድ ገሃድ የቃሉ ትርጉም መገለጥ መታየት ነው። በጥምቀት መገለጥ መባሉ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ 30 ዓመት እድሜው በባሕረ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" በማለቱ መንፈስ ውዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ በነቢያት አምላክ ይወርዳል ይወለዳል ይሰቀላል ይሞታል ይነሳል ብለው የተናገሩለት መሲሁ እሱ መሆኑ ተገልጧል እንዲሁም ሦስቱ አካላት (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) ታይተዋልና ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ገሃድ ይባላል የገሃድ ጾም ጥር 10 ቀን ለ11 አጥቢያ ነው 7. ጾመ ፍልሰታ ይህን ጾም ለመጀመሪያ ጊዜ የጾሙት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ በአሁን ጊዜ ግን ከሕጻን (7ዓመት ጀምሮ) እስከ ሽማግሌ ድረስ የሚጾሙት ጾም ነው የሚጀምረው ነሐሴ 1 ሲሆን በ16 ይፈታል እመቤታችንን ልጇ ጌታችን ኢየሱስ በስልጣኑ ከሞት ማስነሳቱ እና የዕርገቷ መታሰቢያ በዓል ነው
Dec 02, 2024