Selam endet nachu. Ye genan tsom lemn endemitsom btnegrugn? Amesegnalew 😊
Nov 25, 2024💮 ✝️ ጾመ ነብያት ✝️ 💮 ➡️ ጾመ ነቢያት የገና ጾም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ከህዳር ፲፭ 15 ጀምሮ ለ ፵፫ 43 ቀናት የሚጾም ሲሆን ፋሲካው ፍቺው በልደት በዓል ነው፡፡ ይህም ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ቅዱሳንና ምዕመናን ጾመውታል፡፡ ➡️ ጾመ ነብያት ስያሜውን ያገኘው ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለተፈጸመበት ነው፡፡ በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምስጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ ፣ የረቀቀው ገዝፎ ጎልቶ እየተመለከቱ ትንቢት ተናገሩ ፤ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ጾሙ ጸለዩ፡፡ ➡️ ነቢያት ከእመቤታችን ስለ መወለዱ ፥ ወደ ግብፅ ስለ መሰደዱ ፥ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ ፥ ብርሃን በሆነው ትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ ፥ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ ፥ ስለ ትንሣኤው ፥ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፡፡ ለአዳም የተሠጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው ፦ "አንሥእ ኃይልከ ፣ ፈኑ እዴከ" እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም እግዚአብሔር ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት ፣ በሳምንታት ፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ፬፵፮ ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡ ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር ፦ "አያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር" ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩ እነ ነቢዩ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ ኢሳ.፶፰፥፩፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለተፈጸመበት ይህ ጾም "የነቢያት ጾም" ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ስለሆነም "ጾመ ስብከት" ይባላል፡፡ ➦ ጾመ ነቢያት፦ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው ፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች : ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም : ቅዱስ ሙሴ : ቅዱስ ኤልያስ ፣ ቅዱስ ዳንኤልና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: ዘዳ.፱፥፲፱ ፣ ነገ.፲፱፥፰ ፣ ዳን.፱፥፫ መዝ.፷፰፥፲ ፻፰፥፳፬ ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል:: ❤️ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Nov 25, 2024