🌺የያዕቆብ ሌሊት ይኹንልን ማለት ምን ማለት ነው? ☘ብዙውን ጊዜ በተለይ እኛ ክርስቲያኖች ማታ ልንተኛ ስንል ወይም በሰላም እደሩ ከተባባል በኋላ የያዕቆብ ሌሊት ያድርግላችሁ ወይም የያዕቆብ ሌሊት ይሁንላቹ እንባባላለን። ለምን የያዕቆብ ሌሊት.....? ቃሉ ሙሉ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ነው ሁላችንም እንደምናውቀው ቅድስት ቤተክርስቲያን የሁሉ ነገር መሠረቷ መጽሐፍ ቅዱስ ነውና። 🌺ታሪኩ በአጭሩ ስንመለከት የብዙዎች አባት የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ሁለት ልጆች ነበሩት። ኤሳውና ያዕቆብ። ኤሳው ታላቅ ሲሆን ያዕቆብ ታናሽ ነበር። አባታቸው ይስሐቅ በጣም አርጅቶ ስለነበር ታላቅ ልጁን ኤሳውን ሊባርከው ፈልጎ ትዕዛዝ ሰጠው። ትዕዛዙን ለመፈጸም በሄደበት ጊዜ ታናሹ ያዕቆብ እሱን መስሎ ወደ አባቱ ቀርቦ ቡራኬውን ከአባቱ ተቀበለ። ☘በዚህም ምክንያት ኤሳው በጣም ተቆጣ፤ ኤሳውም በዚህ እጅግ ተናድዶ አንዴ ብኩርናዬን አሁን ደግሞ ቡራኬዬን በረከቴን ወሰደብኝ ብሎ እጅግ ተቆጥቶ ነበርና እናቱ ርብቃና አባቱ ይስሐቅም የኤሳው ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ያዕቆብን ከቤርሳቤህ ወደ ካራን ሰደዱት። (ሙሉ ታሪኩን በዘፍ.28፥1- ፍጻሜው ያንብቡት) 🌺ዘፍ.28፥10-ፍጻሜው ስንመለከት ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወደ ካራን ሄደ ብሎ ይጀምራል። ወደ አንድ ስፍራ ሲደርስ ፀሐይ ጠልቃ ስለነበር ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ። በዚህ ሰዓት ነበር ታዲያ እነዚህን ድንቅ ነገሮች በሕልሙ የተመለከተው:- ☘፩. አንዲት መሠላል ራሷ ሰማይ የሚደርስ መላእክት ሲወጡባትና ሲወርዱባት ተመለከተ። መሰላሏም የእመቤታችን ምሳሌ ነች። ያዕቆብ መላእክት ወደ ሰማይ ሲወርዱበትና ሲወጡበት የተመለከታት መሰላል አንቺ ነሽ እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም በእሑድ ሰንበት ውዳሴ ማርያም። 🌺፪. ልዑል እግዚአብሔር አብዝቶ ሲባርከው ተመልክቷል። ☘ስለሆነም የያዕቆብ ሌሊት ይሁንላችሁ ሲባል እንደ ያዕቆብ ድንቅ ሕልም የምታዩበት ድንቅ ሌሊት ይሁንላችሁ ማለት ነው። 🌺ሁሉም ሌሊቶቻችሁ የያዕቆብ ሌሊት ይሁኑላችሁ። 🕊ወስብሐት ለእግዚአብሔር🕊
Jul 17, 2024