በሰሞነ_ሕማማት የሚጸለዩት እና የማይጸለዩት ጸሎቶች የትኞቹ ናቸው? እንደ ቅድስት ቤተ-ክርስትያናችን ሥርዓት በዚህ በሰሞነ ሕማማት የምንጸልያቸውና ለጊዜው የምንታቀባቸው ጸሎቶች አሉ። 👉 በሰሞነ ሕማማት የምንጸልያቸው ጸሎቶች የትኞቹ ናቸው? 📖 ውዳሴ ማርያም እመቤታችን በዚህ በሰሞነ ሕማም በልጅዋ ምክንያት ብዙ እንግልት ስለደረሰባት የእሷን ምስጋና የሆነውን ውዳሴ ማርያም አናስታጉልም። ውዳሴ ማርያም ማመስገኛ መማጸኛ ስለሆነ እንጸልያለን። ምክንያቱም በዚህ በሰሞነ ሕማማት መከራ ተቀብሎ ሞቶ ሕይወቱን የሰጠንን ጌታ በሥጋ ወልዳለችን በውዳሴዋ እናስባታለን። 📖 ዳዊት የቅዱስ ዳዊት ድርሰት የሆነው ታላቁ መዝሙረ ዳዊት በትንቢት ክፍሉ ስለ ጌታችን ሕማም ስቃይ እና ሞት የሚናገርና በዳዊት ምስጋና በምድር የሰው ልጆች በሰማይ ቅዱሳን መላእክት ስለሚያመሰግኑ እንጸልየዋለን። 📖 ሰይፈ ሥላሴ ሰይፈ ሥላሴ ከሦስቱ አካላት እግዚአብሔር ወልድን የሚያመሰግን አምላክነቱን የሚመሰክር እና የሚመሰጥር በመሆኑ እንጸልየዋለን። 📖 ሰይፈ መለኮት ሰይፈ መለኮት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ስለ ምስጢረ መለኮት እና ስለ ጌታችን አምላክነት ስለሚናገር እንጸልየዋለን። 📖 ድርሳነ ማሕየዊ ድርሳነ ማሕየዊ በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ-ነጎድጓድ የዓይን እማኝነት እና የቃል ምስክርነት የተጻፈና የጌታችንን መከራ ስቃይ እንግልት እና ሞት በልዩ ሁኔታ የሚናገር በመሆኑ ልክ እንደ ውዳሴ ማርየም የየእለት/የየቀን ስላለው ብንጸልየው በዓይነ ሕሊና ቀራንዮ ወሰዶ በነፍሳችን የጌታችንን ሰማያዊ ውለታ የሚስልብንና በመጸለያችን ልዩ ጸጋና ክብር የሚያሰጥ የቃል-ኪዳን ጸሎት በመሆኑ በዚህ በሰሞነ ሕማማት ብንጸልየው እጅጉን እንጠቀምበታለን። 📖 ውዳሴ አምላክ የጌታችን ምስጋና በመሆኑ መጸለይ እንችላለን። 👉 በሰሞነ ሕማማት የማይጸለዩት ጸሎቶች የትኞቹ ናቸው? በሰሞነ ሕማማት የማይጸለዩትን ጸሎቶች ጠቅለል አድርገን ስናያቸው 📕 ድርሳናት 📕 ገድላት 📕 መልኮች ናቸው። ይህም የሆነው በሰሞነ ሕማማት ጌታችን ለእኛ ለሰው ልጆች ብሎ የተቀበላቸውን ስቃይ እና መከራ ሞት የምናስብበት እና የምናለቅስበት እንጂ ሌሎቹን በድርሳናቸው በገድላቸው በመልካቸው የምናመሰግንበት ጊዜ ስላልሆነ ነው።
May 02, 2024