Selam My question is for..Orthodox emnet tektay (የዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 19) ---------- 9፤ እርሱም። ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም። ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ። 10፤ ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም። እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ። please asrdugn sewoch teykewgn new endet new yehen yemtrdute??
Oct 25, 2023ራእይ 19፡10 “ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ እርሱም እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ” ራእይ 22፡8-9 “ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ፡፡ በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ፡፡ እርሱም እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ፡፡” ሁለቱን ጥቅሶች ከመተንተናችን በፊት ‹መልአኩ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ” ሲል ሁለት ጊዜ ከልክሎታልና ለመላእክት ስግደት አይገባም› የሚሉ ወገኖች ጥያቄያቸው ስሕተት መሆኑን (አጠያየቁ ራሱ ማስተዋል የሌለበት መሆኑን) ለማመልከት ሦስት አመክንዮአዊ ነጥቦችን ላንሣ፡፡ 1ኛ. ለመላእክት የሰገዱ ቅዱሳን ብዙ ሆነው ሳለ ዮሐንስን ብቻ መልአኩ እንዳይሰግድ ጠይቆታል፡፡ በቁጥር ደረጃ ስናየውም ለመላእክት ሰግደው ያልተከለከሉት ብዙ ናቸው፡፡ ከላይ ካነሣናቸው እንኳን በለዓም ፣ ኢያሱና ዳንኤል በመስገዳቸው ተባርከዋል፡፡ ሎጥም እንዲሁ (ዘፍ. 19)፡፡ ዮሐንስ መናፍቃኑ እንዳሰቡት መስገዱ ስሕተት ነው ቢባል እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ አትስገድ የተባለ አንድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ (መስገዱ ግን ስሕተት አለመሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው)፡፡ ሌሎቹ ግን መስገዳቸው አስባርኳቸዋል፡፡ ስለዚህ አንድ ቅን ሰው ይህን የሚጠይቀው ‹ሌሎቹ ቅዱሳን ሲሰግዱ ያልተከለከሉበት ዮሐንስ ግን የተከለከለበት ምክንያት ምን ይሆን› ብሎ ነው እንጂ እንዲሁ ‹ዮሐንስ አትስገድ ስለተባለ አልሰግድም› በማለት አይደለም፡፡ እንዲህማ ከሆነ እኛም ‹በለዓም አትስገድ ስላልተባለ እንሰግዳለን› ፣ ‹ኢያሱ ሰግዶ ስለተባረከ እንሰግዳለን› ፣ ‹ዳንኤል ሰግዶ ስለተዳሰሰ እንሰግዳለን› በማለት ብቻ ከእነርሱ ይልቅ በብዙ ምሳሌዎች የታጀበ መልስን መስጠት እንችል ነበር፡፡ ዓላማችን ግን እነርሱንም መመለስ ነውና ዮሐንስ አትስገድ የተባለበትም ምክንያት እነርሱ እንደሚያስቡት ለመላእክት ስግደት ስለማይገባ እንዳልሆነ እናሳያለን፡፡ 2ኛ. መልአኩ ለእርሱ በተገለጠለት በፍጥሞ ደሴት ሳለ ራእዩን ሲመለከት በመንፈስ ቅዱስ በተቃኘ አገልግሎት ውስጥ ነበር፤ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ” (ራእይ 1፡10) ብሏልና፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ ለመላእክት ስግደት ሳይገባ ሰግዷል ካልን የሰገደው በስሕተት ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ‹በመንፈስ ነበርሁ› ብሎ ነበርና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ተሳስቶ አሰገደው ወደሚል ክህደት ይመራናል፡፡ በመንፈስ የሆነ ሰው ከማይሳሳተው ቅዱስ መንፈስ ጋር ነውና የሚሠራው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ በመንፈስ የነበረው ዮሐንስም በመንፈስ በነበረበት ጊዜ የሠራው ሁሉ ልክ ነበር፡፡ መስገዱም ልክ ነበር፡፡ አንዳንድ የዋሕ ምእመናንና መምህራንም ይህንን ባለመረዳት ‹ዮሐንስ በስሕተት ለአምላክ የሚገባ የባሕሪይ ስግደትን ለመልአኩ ስለሰገደለት መልአኩ ገሰፀው› ብለው ይሳሳታሉ፡፡ ሆኖም ይህ አባባል ስሕተት ነው፡፡ ቅዱሱ ሐዋርያ ለክርስቶስ የሚገባን ስግደትና ለመልአክ የሚገባን ስግደት የሚያውቅ ጻድቅ ነው፡፡ መስገዱም ትክክል ነው፡፡ 3ኛ. ቅዱስ ዮሐንስ ተሳስቶ ሰገደና መልአኩ ገሰፀው ብንል እንኳን መድገሙ ስለምንድን ነው ልንል ነው? ስሕተት የሆነ ከሆነ እንደ ሐዋርያነቱ ፈጥኖ ‹ስሕተቱን› በማረም ለሁለተኛ ጊዜ አለመስገድ ነበረበት፡፡ መልአኩ ያለውን አልቀበል ብሎ ከሆነም መልአኩ መቅጣት ነበረበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን መላእክት የተናገሩትን አልሰማ ያሏቸውን ቅዱሳን ሲቀጡ ዐሳይቶናል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ የመልአኩን ቃል ባለመስማቱ ካህኑ ዘካሪያስ ተቀጥቷል፡፡ “መልአኩም መልሶ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም፡፡” (ሉቃ.1፡19-20)፡፡ ታዲያ ዮሐንስስ ተሳስቶ ከሆነ አትስገድ ተብሎ እንደገና ሲሰግድ ለምን አልተቀጣም? ነው ወይስ የእግዚአብሔር ፍርድ ከሰው ወደሰው ይለያያል? በስሕተት ደረጃ ካየነው እኮ ከዘካሪያስ ይልቅ አትስገድ ተብሎ መስገድ ይብሳል፡፡ እንዲያውም በመለኮቱ የሚመጡበትን የማይወደውን እግዚአብሔርን ማስቆጣትና የእርሱን ስግደት ለሌላ መስጠት ነው፡፡ የዘካሪያስ ግን ይህ ይሆንልሃል ብቻ ነው የተባለው፡፡ እርሱም ቢሆን እንዴት ይሆናል አርጅቻለሁ እኮ ብሎ በመጠራጠር ተከራከረ እንጂ አይሆንም አላለም፡፡ ዮሐንስ ግን ስግደቱ እኮ ላንተ ይገባል ብሎ ሳይከራከር ደግሞ ሰገደ፡፡ ታዲያ ተሳስቶ ቢሆን የዮሐንስ የበለጠ ድፍረት አይደለምን? ነገር ግን መስገዱ ልክ ስለነበር መልአኩም እንዳይሰግድለት ጠየቀው እንጂ አላገደውም፡፡ ††† ታዲያ መልአኩ ከሌሎች ለይቶ ዮሐንስን ለምን እንዳይሰግድ ጠየቀው? ††† ሌሎች ቅዱሳን ለመላእክት ሲሰግዱ ያልተከለከሉት ዮሐንስ ግን እንዳይሰግድ የተጠየቀው ስለ ክብሩ ነው፡፡ ዮሐንስ ከሌሎቹ ለመላእክት ከሰገዱት ቅዱሳን ይልቅ የከበረና ከመላእክት ጋር የተካከለ ነው፡፡ ስለዚህ ‹የምትተካከለኝ ወይም የምትበልጠኝ ሆነህ ለኔ መስገድ አይገባህም› ሲል ስለ ትሕትና መልአኩ ዮሐንስን ‹እንዳታደርገው ተጠንቀቅ› አለው፡፡
Oct 26, 2023