ሰው ሰራሽ ክህሎት (Artificial Intelligence) ማለት የሰውን ጉብዝና (ችሎታ) (Cognitive Skill) ለሮቦት ወይም ለማሽን ሰጥቶ አንድን ስራ እንዲያከናውን የሚሞክር የቴክኖሎጂ ጥናት ዘርፍ ነው። ለምሳሌ አንድ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ ያለ የመኪና ገጣጣሚ ባለሙያ የሆነ ሰው መኪናዎችን እንዴት መጋጣጠም እንደሚችል አስቀድሞ ከተማረ እና እዉቀት ካዳበረ በኋላ መኪናዎችን ይገጣጥማል። በተጨማሪም ይህ ተፈጥሯዊው ሰው ስሜት እና ፈቃድ አለው። ሰዎች ብቻ ያላቸው ስሜት እና ፈቃድ ተፈጥሯዊ ክህሎት (Natural Intelligence) ይባላል። ልክ እንዲሁ በተመሳሳይ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ ያለ የመኪና ገጣጣሚ ማሽን ተፈጥሯዊው ሰው እንደሚሰራው ዓይነት የመኪና መጋጣጠም ስራ ይሰራል። እንደ ተፈጥሯዊው ሰው ይህ የመኪና ገጣጣሚ ማሽን መኪናዎችን እንዴት መጋጣጠም እንደሚችል አስቀድሞ ከተማረ እና እዉቀት ካዳበረ በኋላ መኪናዎችን ይገጣጥማል። እኛ ተፈጥሯዊ ሰዎች እዉቀት የምናዳበረው በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ፊደል በመቁጥር እና መፅሐፍትን በማንበብ ነው። ታዲያ “እንዚህ ሰው ሰራሽ ሮቦቶች እና ማሽኖች እንዴት ተማሩ፤ እወቁ፤ እዉቀት አዳበሩ?” የሚለው ጥያቄ ሰው ሰራሽ ክህሎትን (Artificial Intelligence) ይመልስልናል። እንዚህ ሰው ሰራሽ ሮቦቶች እና ማሽኖች በተለያዩ የኮምፐውተር ስልት አማካኝነት የሰውን ጉብዝና (Cognitive Skill) ዓይነት ችሎታ ይማራሉ። ለእነዚህ ሮቦቶች እና ማሽኖች የተለያዪ ካሜራዎች እና ሴንሰሮች ይገጠሙላቸዋል። እነዚህ ካሜራዎች እና ሴንሰሮች ሮቦቶቹ እና ማሽኖቹ ማየት፤ መጫን እና መለካት እንዲችሉ ያግዟቸዋል። በዚህ አማካኝነት ሮቦቶቹ እና ማሽኖቹ እንደዉም ከተፈጥሯዊው ሰው በተሻለ ፍጥነት፣ ብቃት እና ቅልጥፍና፤ የኃይል ምንጭ አይቋረጥባቸው እንጂ ያለድካምም ጭምር መኪናዎችን ይገጣጥማሉ፤ ተግባራቶችን ይከውናሉ። ነገር ግን እነዚህ ሮቦቶች እና ማሽኖች ከተፈጥሯዊ ሰው ለየት የሚያደርጋቸው ስሜት እና ፈቃድ የላቸውም። አያዝኑም፤ አይደሰቱም፣ አይስቁም። ስለዚህ ሰው ሰራሽ ክህሎት (Artificial Intelligence) ስሜትን እና ፈቃድን አያካትትም። ሮቦት አንድ አካል ያለው ቁስ ሲሆን ሰው ሰራሽ ክህሎት (Artificial Intelligence) ደግሞ ለዚህ አካል ላለው ቁስ እንዴት ነገሮችን ማከናውን እደሚችል የመስራት እውቅት ይሰጣል። © axum. ai
Jul 16, 2023