Selam sewoch Esti Orthodox ena tewahdo mn malet endehone tirgumun bedenb asredugh🙏🙏
Apr 22, 2023መልስ ተዋሕዶ (Miaphysite) ተዋሕዶ የሚለው ቃል ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ነው፡፡ ትርጒሙም “አንድ ሆኖ” ማለት ነው። በዚህ ትርጉም ውስጥ አንድ የሆኑት መለኮታዊና ሰብዓዊ ባሕርይ (መለኮትና ትስብዕት) ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የተዋሕዶ ትርጓሜ በአጭሩ “ወልድ ዋሕድ” የሚለው ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ያለሚጠት (ያለመመለስ)፣ ያለ ውላጤ (ያለ መለወጥ)፣ ያለ ቱሳኤ (ያለ መቀላቀል)፣ ያለትድምርት (ያለ መደመር)፣ ያለ ቡዓዴ (ያለመለያየት)፣ ያለ ኅድረት (ያለ ማደር) ነው፡፡ ክርስቶስ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነው በተዋህዶ ነው፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ የሚለው ቃል ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ምስጢር የሚገልፅ ታላቅ ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው በ ተ ዋ ሕ ዶ ነው! ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (Orthodox Miaphysite) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋህዶ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል ሆነ (ሥግው ቃል ነው) ብላ የምታምን ቀጥተኛና ትክክለኛ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ ይህም ነቢያት የተናገሩትን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ያስተማረውን፣ ሐዋርያት የሰበኩትን፣ ሊቃውንት ያመሠጠሩትን አስተምህሮ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከሐዋርያት (ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች) በቀጥታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈች ከእኛ ትውልድ ስለደረሰች ቀጥተኛ ናት፡፡ ያልተበረዘች ያልተለወጠች ያልተከለሰች ስለሆነችም ትክክለኛዋ እርሷ ናት፡፡ በማቴ 16፡16-18 ላይ “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” ይላል፡፡ ተዋሕዶ (ወልድ ዋሕድ) የሚለው ይህንን የጴጥሮስን እምነት የሚያመለክት ነው፡፡ ጌታችን እንዳረጋገጠው ይህች የጴጥሮስ እምነት ዓለት ናት፡፡ ቤተክርስቲያናችንም በቀጥታ በዚህ እምነት/ዓለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትባለለች፡፡ ይህች ዓለት የምትለወጥ/የምትታደስ አይደለችም፡፡ ቤት ሲታደስ እንኳን መሠረቱ አይታደስም፡፡ ሃይማኖት መሠረት ነው፡፡ ምግባር ደግሞ ግድግዳና ጣሪያ ነው፡፡ ቤት ቢያረጅ ጣሪያና ግድግዳው እንጂ መሠረቱ አይታደስም፡፡ መሠረቱን ለማደስ መሞከር ቤቱን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ እንደገና መሥራት ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ኛ ቆሮ 3:11)።” ይላል፡፡ በዚህ መሠረትነት ላይ የጸናች ሃይማኖት ሰውን ታድሳለች እንጂ እርሷ አትታደስም
Apr 23, 2023