ይህ ጥያቄ ለኦርቶዶክስኦች ነው በአሁን ሰአት ላይ ብዙዎቻችን profile picture ያረገነው የተዋህዶ አርማ ላይ መልአኮቹ የያዙት በትር ላይ ሁለት እባቦች አሉ ትርጉሙን ካወቃቹት እባካቹ አስረዱኝ ሰለቀና መልሳቹ አመሰግናለሁ
Feb 07, 2023የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓርማ ምን ያመለክታል? ፩. የዓርማው ቅርጽና ይዘት፥ ፩.፩. መደቡ *ነጭ፤ ፩.፪. ዙሪያው የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ፤ ፩.፫. ከላይ ከአናቱ አክሊል፤ ከታች ከግርጌው መሐል ለመሐል ወጥቶ አናቱ ከአክሊሉ ሥር የደረሰና መስቀል ያለበት ዓርዌ ብርት፤ ፩.፬. በግራ ኹኖ በቀኝ እጁ ዓርዌ ብርት፤ በግራ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ፤ በቀኝ ኹኖ በግራ እጁ ዓርዌ ብርት፤ በቀኝ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ፤ ፩.፭. ከዓርዌ ብርቱ ሥር “ነዋ ወንጌለ መንግሥት” ተብሎ የተጻፈበት ቅዱስ መጽሐፍ፤ ፩.፮. ከቅዱስ መጽሐፍ ሥር መስቀለኛ የ”ጸ” ፊደል ቅርፅን የሚመስል፤ ኹለቱ ጫፎቹ ከመደቡ ወደ ውጭ የወጣ ሰበን፤ ፩.፯. የስንዴ ዛላና የወይን ዘለላ በተገናኙበት የዓለም ምስል፤ ያለበት ይኾናል፡፡ ፪. የዓርማው ትርጉም፥ ሀ/ መደቡ *ነጭ መኾኑ፥ ዘመነ ሥጋዌ የምሕረት፣ የደስታና የነፃነት ዘመን መኾኑን ያመለክታል፤ (ዮሐ.፳፥፲፪፤ የሐዋ. ሥራ ፩፥፲) ለ/ የዓርማው ዙሪያ በወይን ዛላና በስንዴ ዘለላ የተከበበ መኾኑ፥ ምእመናን በቅዱስ ቊርባን አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን፣ ስርየተ ኃጢአትን፣ የዘለዓለም ሕይወትን የሚያገኙ መኾናቸውን ይገልጻል፤ (ዮሐ. ፮፥ ፶፫-፶፰፤ ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ መዝ. ፬፥፯) ሐ/ በዓርማው መሐል ቀጥ ብሎ የቆመ የዓርዌ ብርት ምስል በበላዩ ላይ መስቀል፣ ከዚያም ከፍ ብሎ አክሊለ ክህነት አለው፤ የዚኽ ትርጉም፥ ሕዝበ እስራኤል ዓርዌ ብርቱን ባዩ ጊዜ ከእባብ መርዝ እንደ ዳኑ ኹሉ መስቀል ላይ በተሰቀለ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ኹሉ በዲያቢሎስ ምክንያት ከመጣባቸው ፍዳ ኃጢአት የሚድኑ መኾናቸውን፤ መስቀሉ፥ የቤተ ክርስቲያን የድኅነት ዓርማ መኾኑን፤ (ዘኍ. ፳፩፥፰፤ ዮሐ. ፫፥፲፬) መ/ አክሊል፥ ቅዱሳን በሰማያዊ መንግሥት የሚቀዳጁትን አክሊለ ክብር እና ማኅተመ ጽድቅን ያመለከታል፤ (ዘጸ. ፴፱፥፴፤ ፩ተሰ. ፪፥፲፱፤ ፪ጢሞ. ፬፥፰፤ ፩ጴጥ. ፭፥፲፬፤ ራእይ ፪፥፲፤ ፬፥፲፬) ሠ/ ኹለት መላእክት የዘንባባ ዝንጣፊና ዓርዌ ብርቱን ይዘው ይታያሉ፤ ይህም ዘንባባ፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መንፈሳዊ ደስታንና ድኅነተ ነፍስን ያመለክታል፤ ቅዱሳን መላእክት የቤተ ክርስቲያን ጠባቂዎችና የመልካም ዜና አብሣሪዎች መኾናቸውን ያሳያል፤ ዓርዌ ብርቱን ይዘው መቆማቸው፥ ነገረ መስቀሉን አምኖና ሃይማኖቱን አጽንቶ ይዞ የሚኖር የዘለዓለም ድኅነትን የሚያገኝ መኾኑን ያመለክታል፤ (መዝ. ፺፥፲፩፤ ሉቃ. ፲፫፥፮-፱፤ ዕብ. ፩፥፲፬) ረ/ የዓርማው መሐል ቅዱስ መጽሐፍ ኹኖ፥ “ነዋ ወንጌለ መንግሥት” የሚል ጽሑፍ በበላዩ አለበት፤ የዚኽ ትርጉም፥ የቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖት፣ ቀኖና እና ትውፊት በቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት ላይ የተመሠረተ መኾኑን ያመለክታል፡፡ (ማቴ. ፳፬፥፲፬) ሰ/ ከቅዱስ መጽሐፉ ግርጌ የሚታየው ሰበን፥ ቅድስት ድንግል ማርያም ስታርግ ለቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ የሰጠችውን ሰበን የሚገልጽ ሲኾን፤ ትርጉሙ፥ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤንና ዕርገትን እንደዚኹም የምእመናን እናት መኾኗን የሚያመለክት ነው፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፳፯) ሸ/ የስንዴው ዛላና የወይኑ ዘለላ በተገናኙበት ላይ የሚታየው ክብ ነገር፥ ዓለምን የሚወክል ኾኖ ዓለም በክርስቶስ መዳኑን ያመለክታል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፲፯) ፫. የዓርማው ክብር፥ ሀ/ ዓርማው፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሉዓላዊ ክብር መገለጫና መለያ ስለኾነ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገር የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ጽ/ቤቶች ከዚኽ ዓርማ በቀር ሌላ ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡ ለ/ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ኾኖ ይህ ዓርማ የሌለበት ማኅተምና የማዘዣ ደብዳቤ የሚጠቀም ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጽ/ቤት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምንጭ፤ ሐራ ዘተዋሕዶ *የነጩ መደብ በጥቁር መለወጥ ሰሞኑን ቤተክርስቲያኒቱ በደረሰባት መከራ ምክንያት መሆኑ ነው።
Feb 08, 2023