ሀይማኖታዊ ጥያቄ አዳም እፀ በለስን ከበላ በኋላ ወደ ሲኦል ሲባረር እግዚአብሔር ከ5500 አመት በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ያለበትን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ምዕራፍና ቁጥሩን ንገሩኝ 🙏 አመሠግናለሁ
Sep 14, 2022ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ!!! አዎ ቃል በቃል በተባሉት ቃላት በአንድ ቦታ የተፃፈ ነገር የለም ያ ማለት ግን በጠቅላላ ይሄ አስምህሮ በመፅሐፍ ቅዱስ ዉስጥ የለም ብሎ ማለት እንደማይቻል እና ክርስቲያኖችም እንደዛ ሊሉ እንዴት እንደቻሉ እንመልከት:: በመጀመሪያ ለአዳም ቃል የተገባለት ቦታ በመጀመሪያዉ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ዘፍጥረት ላይ ይገኛል:: እርሱም እንዲህ ይላል:: “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። “ዘፍ 3:15 ይሄ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል እጂግ ጥልቅ ምስጢር ይዟል:: ይሄም ለጊዜዉ አዳምን ፣ ሔዋንና እባብን ይረግማል፣ ፍፃሜዉ እባብን(ሰይጣንን) የሚቀጠቅጠዉ “እርሱ” በማለት ስለ ክርስቶስ ይናገራል:: ራስህን ይቀጠቅጥሃል ማለቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ ሰይጣንን ድል እንደሚያደርግ ሲናገር ነዉ:: እንዲሁም ሰኮናዉን ትቀጠቅጣለህ ሲል ኢየሱስ የተቀበላቸዉን የመስቀል ላይ መከራዎችን ይገልፃል:: በዘርህና በዘርዋ ጠላትነት አደርጋለሁ ሲል በሔዋን ዘርና በሰይጣን መካከል ዘላለማዊ ጥል እንደሚኖር ተናገረን:: አስተዉሉ አዳምና ሔዋን ከተሳሳቱ በኋላ ራቁታቸዉን ሆኑ ፣ ከእግዚአብሔር ፀጋ ተለዩ :: እግዚአብሔር ግን ምንም እንኳን አመፀኞች ና ኃጢአተኞች ቢሆኑም በዝምታ አላያቸዉም:: እንደበደሉት እያወቀ እነሱን ለማልበስ ሲል ፣ እንዳይበርዳቸዉ በማለት ስለፍቅሩ ብቻ ስለነሱ የንፁሐን እንስሳትን ደም ማፍሰስ ጀመረ:: አዳምና ሔዋንን ልብስ ያለብሳቸዉ ዘንድ እንስሳትን ገደለ:: ይሄም :: “እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም።”ዘፍ 3:21 ተብሎ የተፃፈዉ ነዉ:: የነዚህ እንስሳት ቆርበት ልብስ ምሳሌዉ በኋላ አማናዊዉ በግ በሆነዉ በክርስቶስ ኢየሱስ ልብስነት ተፈፅሟል:: ኢየሱስ ክርስቶስ ሊለበስ የሚገባዉ የፀጋ ልብሳችን መሆኑን ቅዱስ ጳዉሎስ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:: “ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።” ሮሜ 13:!4 “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና::” ገላ 3:26 ኢየሱስ ንፁህና ቅዱስ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ በቀራኒዮ አደባባይ ርቃኑን ሆኖ እኛን አለበሰን:: ሌላዉ ጉዳይ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚጠበቅና ተስፋ የሚደረግ ጊዜ እንደነበር ቅዱስ ጳዉሎስ “የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ” በማለት ታቅዶለት የነበረ ዘመን መኖሩን አስረዳን :: እንዲህ ይላል:: “ነገር ግን የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደዉን ከሕግም በታች የተወለደዉን ልጁን ላከ::”ገላ 4:4 እንግዲህ ዋናዉ ቁም ነገር የልጅ ልጅ የሚለዉን ማግኘት ነዉ ::አሁን የሰይጣንን ራስ የሚቀጠቅጠዉ ተናፋቂዉ መሲህ እንደሚመጣ አይተናል:: የልጅ ልጅ የሚለዉን ለምትፈልጉ ይሄዉ ብለናል:: “ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥ የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊም ልጅ ፣የናጌ ልጅ፥ የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮዳ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ የዮሳስ ልጅ፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ የዳዊት ልጅ፥ የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ የነአሶን ልጅ፥ የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ የናኮር ልጅ፥ የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥ የቃይንም ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥ የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ የመላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ። ”ሉቃ 3:23-33 በቃ ቤተ ክርስቲያን ከየትም አላመጣችዉም ከላይ ያለዉን የዘር ሐረግ ከመሸምደድ በአጭር ቋንቋ ለመግለፅ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ብሏል:: በማለት ታስተምራለች::
Sep 15, 2022