አስሩ መንፈሳዊ ማዕረጋት ================ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ሲኖር በቅድስናና በንጽህና እያደገ ሲመጣ የሚደርስባቸው አስር መንፈሳዊ ማዕረጋት አሉ፡፡ እነዚህ አስር መንፈሳዊ ማዕረጋት በሦስት የሚከፈሉ ሲሆን፡- ንጽሐ ሥጋ፤ ንጸሐ ነፍስና፤ ንጽሐ ልቡና ይባላሉ፡፡ ከዚህ በመቀጠል አስሩንም ማዕረጋት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ 1. ጽማዌ፡- -------------- ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን ትህትናን፤ ራስን ዝቅ ማድረግን፤ መታገስን እና ነገሮችን በውስጥ ይዞ ማሰላሰልን ወዘተ…ይይዛል፡፡ እዚህ ደረጃ የደረሰ ሰው የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላል በብዙ ነገሮች ላይ ዝምታን ይመርጣል፡፡ 2. ልባዌ፡- -------------- ይህ ማስተዋልና ልብ ማለትን ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች የሚገኙበት ደረጃ ነው፡፡ እዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ሰዎች ልናገር ሳይሆን ልስማ፤ ላስተምር ሳይሆን ልማር ይላሉ፡፡ የመጽሐፉ ቃል የሚለውን ማስተዋል እና አብዝተው ሀጢአታቸውን ያሰላስላሉ ማስተዋልን ገንዘብ ያደርጋሉ፡፡ 3. ጣዕመ ዝማሬ፡- ------------------------- እዚህ ደረጃ የደረሰ ሰው አንደበቱን ከንባብ ልቡናውን ከምስጢር ያቆራኛል፡፡ እዚህ ደረጃ የደረሱ ቅዱሳን አንደበታቸው ዝም ቢል በልባቸው ግን ዝም ብለው አያውቁም ከሰውነታቸውም ንጽሕና አይለይም፡፡ የሚያነቡትን መጽሐፍና የሚጸልዩትን ጸሎት ምሥጢሩን በደንብ እየተረዱት ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ እነዚህ ከ1-3 ያሉት የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት ናቸው፡፡ 4. አንብዕ፡- --------------- እዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ሰዎች የጌታቸውን ፍቅር እያሰቡ እስከሞትና መከራ የተጓዘውን ጉዞ እያሰቡ ዘወትር ያለቅሳሉ፡፡ ያለምንም ተጽዕኖ እንባቸው እንደውሀ ይወርዳል፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ለዚህ ዓለም ፍላጎታቸው መሟላት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረትና ቸርነት በመናፈቅ ነው፡፡ 5. ኩነኔ፡- -------------- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል፤ ነፍስ በሥጋ ፍላጎት ላይ ትሰለጥናለች፡፡ ምድራዊ (ሥጋዊ) ፍላጎቶች ይጠፉና ሰማያዊ (የነፍስ) ፍላጎቶች ቦታውን ይወርሳል፡፡ 6. ፍቅር፡- -------------- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ማንንም ሳይመርጡ ወዳጅንም ጠላትንም መውደድ ይጀምራሉ፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ያደረገውን ታላቁን የፍቅር ሥራ እርሱን በመምሰል በሕይወት በመኖር በተግባር ይገልጻሉ፡፡ 7. ሁሰት፡- -------------- ከዚህ ማዕረግ የደረሱ ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሆነው ሁሉን ነገር ማየት ይችላሉ፡፡ የቦታ ርቀት እና የገዘፉ ቁሶች ሳያግዳቸው፤ ሁሉን ያያሉ፡፡ እነዚህ ከ4-7 ያሉት የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት ናቸው፡፡ 8. ንጻሬ መላዕክት፡- --------------------------- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ መላዕክትን ሲወጡና ሲወርዱ ማየት ይቻላል፡፡ 9. ተሰጥሞ፡- ---------------- ከዚህ ማዕረግ የደረሰ ሰው በብርሃን ባሕር እየተመላለሰ በምድሪቱ ላይ ያለውን ሁሉ ማወቅ መረዳትና መመልከት ከመቻላቸውም አልፈው ሥሉስ ቅዱስ ከመመልከት በስተቀር በሰማያት ያለውንም ምሥጢር ወደ መረዳት ይደርሳሉ፡፡ 10. ማዕረገ ከዊነ እሳት/ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- -------------------------------------------------------------- ከዚህ ማዕረግ የደረሱ ሰዎች ሥላሴን በዙፋኑ ላይ ሆኖ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ መመልከት ይጀምራሉ፡፡ እንዲሁም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በአካለ ነፍስ ተነጥቀው ወደ ሰማያት በመውጣት ሰማያትን መጎብኘት ወደ መቻል ይደርሳሉ፡፡ እነዚህን ማዕረጋት አልፈው ቅዱሳን ገና አልበቃሁም ይላሉ በትህትና በፍቅርና በእምነት ሆነው ፤ ከአበው አብርሃም ሥላሴን በነጽሮተ ሰብዕ አይቷል፣ ከነቢያት እነ ኢሳይያስ እና ሕዝቅኤል እግዚአብሔርን በአምሳለ ንጉሥ በዙፋን ላይ ተቀምጦ አይተዋል ፤ አብርሃም እኔ አመድና ትቢያ ነኝ አለ ኢሳይያስም ወዮውልኝ እኔ አልተገባሁም አለ በአማን መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ።
May 18, 2022