#ከኔታ_ኃይለማርያም_ዘውዱ_መልዕክት #ለጥያቄዎቻችን_መልስ #ጾመ ገሃድ/ጋድ? ገሃድ፡- መገለጥ፣ ማታየት፣ መታወቅ፣ ማለት ሲሆን፤ ጋድ፡- ማለት ደግሞ ምትክ፣ ለውጥ፣ ቅያሬ ማለት ነው፡፡ በዓለ ልደት በመጣ ጊዜ ሁሉ በተለይም በዓሉ ዓርብና ረቡዕ ከዋለ ጥያቄዎች ይበዛሉ፡፡ የጥያቄው ምክንያት ደግሞ ደንታቢስነት፣ አለመማር፣ ጥያቄን እንጂ መልስን አለመያዝ ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን ስለ ሰባቱ አጽዋማት በቂ ዕውቀት መያዝ አለበት፡፡ ትምህርቱም ከአንድ ቀን የማያልፍ ግፋ ቢል በሁለት ቀን ቁጭብሎ መማር በሚገባ ሊታወቅ የሚችል ቀላል ትምህርት ነው፡፡ አብዛህኛው ክርስቲያን ግን ለሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚሰጠው ጊዜና ትኩረት ዝቅ ያለና በደንታ ቢስነት የተመላ ስለሚሆን እንደዚህ ያሉ ቀላል ጉዳዮች ሳይቀሩ በየዓመቱ ጥያቄ ሁነው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ ወቅሶ ከማለፍ ድርሻን መወጣት ይሻላልና ቀላል ትምህርት ነው ያልኩትን ጾም ከተነሣሁበት ከገሃድ ጀምሬ ለማብራራት ልሞክር ሰባት ዓመት የሞላው ጤነኛ ክርስቲያን ሊጾማቸው የታዘዙ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ እነርሱም 1. ገሃድ/ ጋድ ትርጉሙን ከላይ ስላስቀመጥኩት ወደምሥጢሩ ስገባ ይህ ጾም የልደትና የጥምቀጥ ማዜማ ነው ፍትሐ ነገሥቱ አንቀጽ 15 ቁጥር567 ላይ ‹‹ እንደ ዐቢይ ጾም በመጠንቀቅ የሚጾም አለ ብሎ ሌሎቹን ከዘረዘረ በኋላ…ወጾመ ድራረ ልደት ወጾመ ድራረ ጥምቀት፡- የልደትና የትምቀት ዋዜማ ጾም ነው ይላል፡፡ አንዳንዶች በጾም ላይ ጾም የለምና ለገና ጋድ የለውም ለማለት ይሞክራሉ ቁምነገሩ ግን ጾሙን ደርበን ሳይሆን ለብቻ አንድ ዕለት ጨምረን ነው እየጾምን ያለንው፡፡ ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 28 ያለው ቀን ሲቆጠር 44 ነው፡፡ ይኸውም 40ው የነቢያት ጾም ነው ሦስቱ ቀናት አንዱ የመበሥር የጌታ፣ ሁለተኛው የተበሣሪ የእመቤታችን ሦስተኛው የአብሣሪ የቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በሌላ መንገድ ሦስቱ ቀን የአብርሃም ሦርያዊ ጾም ነው፡፡ ይህ አባት በሦስት ቀን ሱባኤ ተራራ ማፍለሱን ታኅሣሥ 6 የሚነበበው ስንክሳር ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ከ44ቱ ቀናት 40ው የነቢያት፣ ሦስቱ የጌታ፣ የእመቤታችን፣ የቅዱስ ገብርኤል/የአብርሃም ሦርያዊ/ የፊልጶስ ደቀመዛሙርቱ ሊቀብሩት ሥጋው ተሠውሮባቸው ሦስት ቀን ጹመው ያገኙበት/፣ 44ኛዋ ቀን ግን ያለምን ተቀናቃኝ ገሃድ ወይም ጋድ ናት፡፡ ገሃድ መገለጥ ነው በባሕርየ መለኮቱ የማይታየው ጌታ በተዋሕዶተ ትስብእት ስለተገለጠልን መቀበያ አድርገን እንጾመዋለን። ጋድ ባለው ግን የጥምቀትና የልደት በዓል ዓርብና ረቡዕ ቢውሉ ጾም የለምና ለዚያ ምትክ ማለት ነው፡፡ ይህንን ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር566 እንዲህ ይገልጾታል (ወዓዲ ረቡዐ ወዓረበ በኵሉ ሱባኤ ዘእበለ መዋዕለ ሃምሳ ወበዓለ ልደት ወጥመቀት ሶበ ኀብሩ ቦሙ፡- ዳግመኛም ረቡና ዓርብን በየሳምንቱ ሊጾሙ ይገባል፤ ከበዓለ ሃምሳ በስተቀር እንዲሁም ልደትና ጥምቀት ጊዜ ገጥሟቸው ረቡና ዓርብ ከሚውሉበት ጊዜ በቅር፡፡) ከዚህ የምንረዳው ልደትና ጥምቀት ዓርብና ረቡዕ ሲውሉ ጾም አለመኖሩን ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በምትካቸው አንድ ቀን የምንጾምላቸው መሆኑ ነው፡፡ የጥር 11 ቀን ስንክሳርም እንዲህ ይላል ከላይ የገሃድን ነገር እያብራራ ከመጣ በኋላ …በዚች ዕለት ምእመናን እስከምሽት እንዲጾሙ ያዘዙበት ፣ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ የልደትና የጥምቀት በዓል በረዱዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የትሉላት መብል(ሥጋ ወተት ዕንቁላል) በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በዓሉን እንዲያከብሩ የከበሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓላት ናቸውና፡፡ እኛ በዚህ በኃላፊው ዓለም ተድላ ደስታ ደስ የሚለን እንዳይመስላቸው እንደ አይሁድና እንደ አረማውያን በዓል በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳናደርግ ስለዚህ ከልደትና ከጥምቀት በዓል በዋዜማ ያሉትን ሁለቱን ዕለታት እንድንጾም አዘዙን…እያለ ይቀጥላ፡፡ ይህ ሁኖ ሳለ አንዳንድ ሰዎች በዚሁ በጥር 11 ቀን ስንክሳር መጨረሻ ላይ ያለውን አርኬ ጠቀሰው ከላይ የተነበበውን ሙሉ ንባን ዘንግተውና ትተው ለገና ገሃድ የለውም ለማለት ‹‹ ሰላም እብል ለጾመ ዕለት ዋሕድ፤ ዘስሙ ገሃድ፡- ስሙ ገሃድ ለሚባል የአንድ ቀን ጾም ሰላም እላለሁ የሚለውን ይጠቅሳሉ ጥቅሱ ቁርበተ ነክ ነው ሙሉ ስንክሳሩ ሲነበብ አንቀላፍቶ ወይም ስንክሳሩን ሳይሰማ ከአርኬው ብቻ ለደረሰ ሰው ይመስለዋል እንጂ የጥር 11ዱ ስንክሳርስ በማያሻማ ሁኔታ በግልጽና በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡ ገሃድም ለለልደትም ለጥምቀትም የተሠራ ነው፡፡ ዋሕድ ያለው የልደትና የጥምቀጥ ገሃድ አንድ ተብሎ ስለሚቆጠር ነው 44ቱ ጾመ ነቢያት አንድ ተብሎ እንደሚቆጠር፡፡ ገሃድ የሌላቸው ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ፍልሰታ ፋሲካቸው ከረቡዕና ከዓርብ ላይ ሲሆን ይጾማሉ፡፡
Dec 30, 2021